Sunday, 3 July 2016

የፀሎት ቤት Vs የምናምን ቤት





ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ከሀገር ቤት ደውላ የእግዚአብሔርን ቃል በህብረት የምቆርስበት ሁነኛ የፀሎት ቤት ጠቁመኝ ስትለኝ እኔም ብዙ ካወጣሁ ካወረድኩ በኃላ እከሌ ወደሚባለው የፀሎት ቤት እንድትሄድ መከርኳት ("ነብይ" ተብየው መከራዋን አሳያት እንጂ) ፕሮግራሙ ካለቀ በኃላ የነገረችኝን ሳስበው፣ እራሴኑ መልሼ እውነት ግን ወደ ፀሎት ቤት ነው ወይስ ወደ ጠንቋይ ቤት ነው የመራኃት እያልኩ ሳሰላስል፤ ጌታችን ጅራፍ ሲገምድ ባይነ ህሊናዬ ድቅን አለብኝ። 
ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተፅፏል እናንተ ግን.....

ነገሩ መች በወንበዴዎች ቤት ቀረና፤ አሁን ደሞ መልኩን አሻሽሎ አንድ በጠንቋይ ቤት፣ በንግድ ቤት፣ ሲያሻው በዳንኪራ ቤት መገለጥ ከጀመረ ሰነባበተ።

የፀሎት ቤት Vs የጠንቋይ ቤት

ያቺ ከላይ የጠቀስኳት ወዳጄ እንዳለችኝ ከሆነ፣ ሰውየው መድረክ ላይ እየሸለለ እንዲህ ማለት ጀመረ፣ አንድ ሴት አለሽ ባሰሪዎችሽ ውጊያ የበዛብሽ፣ እጅሽን አውጪ፤ የኔ ነገር እስከመቼ እያልሽ ቀን ከሌት የምታነቢ፣ (እስቲ አሁን ይታያችሁ እምባ sale ላይ በወጣበት ሀገር ሰው በቀን ሦስቴ በልቶ ሳይሆን አልቅሶ በሚያድርበት ሀገር እንዲህ ብሎ መልዕክት፤ ምናልባት ሰውየው ጀማሪ "ነብይ" ሳይሆን አይቀርም) ለምልክት ይሆን ዘንድ ቀይ ቀለም ፓንት ነው የለበሽው አለ። (ይሄኔ ነው እንግዲህ ጉባዔው ውስጥ የታደመው ወንድ ሁሉ የልጅቱን ፓንት እያሰበ ወደ ሌላ አለም የገባው። ግማሹ በልቡ፣ ምነው ግን ይሄ አይቶ የተመኘ.....ምናምን የሚለው ቃል ባይኖርና ነብዩ የጀመረልንን Erotic ፊልም ብንጨርስበት ይላል) በመቀጠል ያ ውቃቢ የራቀው ሰውዬ፣ የኔ እህት፣ ስልክ ቁጥርሽን በራዕይ እያየሁት ነው አለና "ከነብይነት" ወደ ቴሌ ሰራተኛነት በመቀየር 0911666....ማለት ሲጀምር፥ ያቺ ሴትዮ ቀዩን ሳይሆን አረንጓዴው ፓንቷ እስኪታይ ድረስ ወለሉ ላይ መንፈራገጥ ጀመረች። (I think "ነብዩ" Colour blind ሳይሆን አይቀርም) ሰውየው ሞቅ አለውና፥ ዛሬ የምታያቸውን ግብፃውያን፥ ለዘላለም አታያቸውም! ሲል፣ ጉባዔው በጩኀት ተናጋ። (ወይ ጉድ! ሰው ይሞታል ሲባል እንዲህ ጮቤ መርገጥ) 

እረ የታለ ያ የየሱስ ጅራፍ?

ከዛማ ምኑ ይወራል? ሰውየው ከግል ካድሬዎቹ የክት ልብስ ላይ ላቡን እየጠረገ፤ ጉባዔውን ባንድ እግሩ ያቆመው ጀመር። 
ሦስት አግብቶ የፈታውን፥ ጌታ በድንቅ እድርሀለሁ ይልሀል ሲለው፤ ሊሞት አንድ ሐሙስ የቀረውን፥ ገና እድሜ አጠግብሀለሁ ብሎ ሲመርቀው፤ በየካፌው ማኪያቶ ሲልጥ የሚውለውን፥ ጌታ ገና ምኑን አይተህ አለምን አዞርሀለሁ ይልሀል ሲለው፤ ኑሮ ከብዷት የፊት ማድያቷ ለሚያሳብቅባት ምስኪን፥ ዘንዶው ተወጋ ሲላት፥ እሷም በምርቃና ብዛት በያዘችው ዣንጥላ ሰው መውጋት ስትጀምር፤ 
ግማሹ፥ ሚሊየነር ትሆናለህ ሲባል፤ እኩሌታው፥ በቤት ላይ ቤት በህንፃ ላይ ህንፃ ትገነባለህ እየተባለ፥ ቤቱን እኛ ሰፈር ያለውን የአዋቂ ቤት አስመሰለው።

የፀሎት ቤት Vs የዳንኪራ ቤት

የኢየሱስን አኗኗር አይቶ የዘመናችንን ቤተክርስቲያን ላስተዋለ፣ ዘንድሮ በፀሎት ቤቱ ውስጥ የሚካሄደው ፀሎት እና ትምህርት ሳይሆን መዝሙር ግርፍ እኔ ፈንጠዝያ ብቻ ነው። ኢየሱስ፦ ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ሲል፥ እኛ ደግሞ በፊናችን፥ ቤቱን የዳንኪራ ቤት አርገነው ቁጭ። በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፥ ኢየሱስ ብዙ ጊዜውን የተጠጠቀመው ለፀሎት፥ ለስብከት እና ለትምህርት ነበር፤ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደዘመረ ተፅፎልናል። (ማቴዎስ 26:30ን ተመልከቱ) እሱ አንዴ ዘምሮ ሺህ ጊዜ ፀለየ፤ እኛ ሺህ ጊዜ እየዘመርን፥ አንዴ እየፀለይን ቤቱን የዳንስ ቤት አርገነው የኢየሱስ ተከታዮች ነን ስንል ግን አናፍርም? ደቀ መዝሙር ማለት እኮ መምህሩን እየተከተለ የሚደቃ ማለት እንጂ የመምህሩን ማዕረግ የሚደቃ ማለት አይደለም። እስቲ በሚመጣው እሁድ ወደየ ፀሎት ቤታችሁ ስትሄዱ ልብ ብላችሁ ለፀሎት እና ለመዝሙር የሚመጣውን ሰው ተመልከቱ። ከዚያም ፀሎት እና መዝሙር ምን ያክል የሰዓት ድርሻ እንደሚሰጣቸው ተመልከቱ። ምን እሱ ብቻ፥ መዝሙር ለመምራት ከሌላ አህጉር ድረስ ሰው እናስመጣለን ፀሎት ለመምራት ግን አለሙ ካልተመቸው ከበደን እንዲመራ እናረገዋለን። ምክንያቱም ቤቱ የመዝሙር እንጂ የፀሎት ከሆነ ቆይቷላ። ለነገሩ አልተኛም ሌሊቱን ቁጭ ብዬ አነጋለሁ የሚሉ ዘማሪዎች በሞሉበት ሀገር ኢየሱስ ሌሊቱን በሙሉ በመዝሙር ሳይሆን በፀሎት እንደሚያነጋው እንዴት እንወቅ? "እርሟን ብታፈላ ስኒ ሙሉ አተላ" አለ አጐቴ። ደሞ እኮ እንዲህ እንቅልፍ አጥተን ሰራነው የሚሉት መዝሙር ቅጠል ቅጠል የሚልና ስሜትን አልፎ መንፈስን የሚነካ አለመሆኑ ነው። አጠጣኅኝ፥ አጐረስከኝ ከሚለው የምግብ ቤት መዝሙራቸው ያለፈውም ቢሆን ነፍሱን ይማርና ከመዝመረ ዳዊት የተቀዳ ነው። ዛሬ መዝሙረ ዳዊት በህይወት ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁሉ እንደ አሸን የፈላ ዘማሪ በቅጂ ወንጀል እስር ቤት እንጂ እግዚአብሔር ቤት አይገኝም ነበር። (ታዲያ ይሄን ስል ሁሉንም ዘማሪዎች እየወረፍኩ አይደለም። ለምሳሌነት ደረጀ ከበደን ማንሳት ከበቂም በላይ ነው)

የፀሎት ቤት Vs የንግድ ቤት

አንድ ወዳጄ ስለ ስራ ሁኔታው ስጠይቀው ባክህ ዘንድሮ ስራ ቀዝቅዟል፣ ዝምብዬ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪውን ብከፍት ነው የሚያዋጣኝ ይለኛል፤ እኔ ደሞ ቀበል አድርጌ፣ ምን? ቦቆሎ ልትዘራ አሰብክ እንዴ? ስለው፥ ምን በወጣኝ እና ነው ከጭቃ ጋር የምታገል? 20 ሰው ሰብስቤ፣ ኪሳችሁ ኪሴ ነው የሚል international church ልከፍት ነው እንጂ አለኝ። ያኔ ነው በየመድረኩ ላይ የሚፈፀመውን ግብይት ማሰላሰል የጀመርኩት፤ የግዜር ቃል ያላግባብ እየተጠቀሰ የኔ ቢጤውን ማራቆት ከተለመደ ቆየ። ጌታችን በሉቃስ 6:38 ላይ የተናገረውን "ስጡ ይሰጣችኋል" የሚለውን ቃል በማጣመምና ህዝቡን በማስገበር ፓስተሩ የህንፃውን መስታወት ያስገጥማል። ትንሽ ከፍ ብላችሁ ስታነቡት ግን ጌታችን እያለ የነበረው ለጠላቶቻችን ሩኅሩኆች ሁኑ ነበር፤ ስጡ ይሰጣችኋል የተባለው ለጠላቶቻችን እንጂ ለፓስተሮቻችን ወይም ለነብያቶቻችን አይደለም። አስራት፥ መባ፥ ስጦታ፥ ዘር እያሉ ስሙን እያቆላመጡ ህዝቡን ያስመነዝሩታል። መች በዚህ አቆሙና፣ በዛው በነካ እጃቸው "ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው" እያሉ እነሱ የራሳቸው መኪና ይሸምታሉ፤ ጳውሎስ ግን በሐዋርያት ስራ 20:35 ላይ የሚያወራው ለድሆች ስለመስጠት እንጂ ለዘማሪዎች አይደለም። ዛሬ ያንተ በስራ መባከን እና ህይወት መድከም ግድ የሚለው የለም ይልቅ አንተ እንኳን ባትመጣ አስራትን ላከው ይልሀል እንጂ። ቤቱን ከፀሎት ቤትነት ወደ ንግድ ቤትነት መቀየር ይሏል እንዲህ ነው። 
*                           *                             *

የእግዚአብሔር ቤት ተጠሪነትዋ ለእግዚአብሔር መንግስት የሆነች ተጠርተው ለወጡ የእግዚአብሔር እንደራሴ (ambassador) የስልጠና እና የፀሎት ማዕከልእንጂ የኛን ሐይማኖት የምናስፋፋባት ቤት አይደለችም። 
ጆሮ ያለው ይስማ።

No comments:

Post a Comment