Sunday, 17 July 2016

"ለወንጌላዊው" ወንጌል ሰበኩለት።



አንድ ጉዳይ ለመፈጠም ከመኀል ከተማ ወደ ሰሜን ምስራቅ የሚወስደውን ባቡር ይዤ፣ ያው እንደሚታወቀው ወቅቱ የሰርግ ስለሆነ ምናልባት ለጓደኞቼ የዘነበው ለኔም ቢያካፋልኝ ብዬ እግረ መንገዴን "ባል የሚስት ራስ ሳይሆን ትራስ ነው" የተሰኘ የትዳር መፅሐፍ እያነበብኩ ሳለሁ ድንገት አንድ ጐልማሳ ቅጥ ባጣ አረማመዱ የማነበውን መፅሐፍ አሽቀንጥሮ ጥሎብኝ ሲያበቃ ይቅርታውን ነፍጐኝ ከፊት ለፊቴ ካለው ወንበር ላይ ተቀመጠ። ወዲያው ፊቷ ብቻ እንዲቀር ተደርጐ እንደ ስጦታ እቃ የተሸፈነች ሴት የሰውየውን ስም ጠርታ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኃላ መጣ ከጐኑ ተቀመጠች።
የሰላምታ ልውውጡ በጭቅጭቅ እንደተጠናቀቀ፥ ልጅቱ እልህ አስጨራሹን የረመዳን ፆም እንዴት እንደጨረሰች ትነግረዋለች፣ በነገሩ ብዙም ደንታ የሌለው የሚመስለው ጐልማሳ ተስፋ በቆረጠ አንደበት እንዲህ አላት፦

አበበ፦ አንች ግን አሁንም ድረስ በቀን አምስቴ እየሰገድሽ ትፆሚያለሽ?

ከድጃ፦ (ብስጭቷን ለመደበቅ እየሞከረች) ምን ማለትህ ነው? ሐይማኖቴ የሚያዘኝን እኮ ነው የማረገው፣ ብትፆም ነበር የፆም ትቅሙ የሚገባህ። ምነው እናንተ ጴንጤዎች አትፆሙም እንዴ?

አበበ፦ እኛ ክርስቶስ ነፃ ስላወጣን ሲያስፈልን ባመቸን ጊዜ ነው የምንፆመው፣ ስራችንን ስለሰራልን እኛ በሱ ማመን ብቻ ነው የሚጠበቅብን። (የሰውየው ንግግር ስላስደነገጠኝ አፍንጫዬን ይነስረኝ ጀመር) 

ከድጃ፦ ኢየሱስ እኮ ጌታ ሳይሆን መልዕክተኛ ስለሆነ ያን ሁሉ ያረገው ለራሱ ነው።

አበበ፦ አንቺ ልጅ ግን የት አምጥተሽ ነው ሁሌ ጌታ አይደለም የምትይኝ? (አለ በንዴት) 

ከድጃ፦ አንተ የት አምጥተህ ነው ኢየሱስ ጌታ ነው የምትለኝ? አሁን ከራሳችሁ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ኢየሱስ ራሱን እኔ ጌታ ነኝ እንድታመልኩኝ ያለበትን ቦታ ካሳየኀኝ አሁኑኑ እኔ ጴንጤ እሆናለሁ። 

(የጥቅስ መዐት ደርድሮ የለበሰችውን ሻሽ እስኪያሶልቃት ለማየት ጓጉቼ አፍ አፉን ማየት ጀመርኩ) ሰውየው ግን የተጠየቀውን ጥያቄ ትቶ ስለ እስልምና መጥፎነት ማውራት ጀመረ...... 

ከድጃ፦ (የጠየቀችውን ትቶ ያልበላውን ሲያክ አብሽቋት) ማን እሱን አውራ አለህ? ለምን ጌታ ነኝ የሚለውን ቦታ አታሳየኝም?

አበበ፦ ከፈለግሽ ስልክ ቁጥርሽን አዲስ አበባ ላለ ነብይ ልስጠውና ደውለሽ አናግሪው፤ ማን እንደሆንሽ፣ ምን እንደምታስቢ ሳይቀር ፈልፍሎ ይነግርሻል። 

ከድጃ፦ ሃሃሃ እረ አልፈልግም! እንዴ ታዲያ እሱ የምን ነብይ ነው ደሞ? ጠንቋይ ነው በለኝ እንጂ! ለማንኛውም ከነብያችን የመጨረሻው ነብይ እንደሆኑ ነው ቅዱስ ቁርዐን የሚናገረው።
(አሁን ይሄ ወንጌል ስርጭት ነው ወይስ ወንጌል ብስጭት? እያልኩ መበሳጨት ጀመርኩ)

አበበ፦ አንቺ ብዙ ያልገባሽ ነገር አለ ስለዚህ ዝምብለሽ አንብቢ! 
ገባሽ አይደል?

ከድጃ፦ ምኑን ነገርከኝና ነው የሚገባኝ? 

አበበ፦ ነገርኩሽ እኮ ለከተማ ወይም ለጨረቃ ከመስገድ ይልቅ ለመስቀሉ መስገድ ይሻልሻል። የሚያድንሽ መሐመድ ሳይሆን ወንጌል ነው። (አለ ቁጣ በተቀላቀለበት ድምፅ) 

ከድጃ፦ (ንዴቱን በፈገግታዋ ለማብረድ እየሞከረች) እኔ መች ነብያችን አዳኝ ናቸው አልኩ? እሳቸው እኮ የአላህ መልዕክተኛ ናቸው። ለመሆኑ ወንጌል ምን ማለት ነው?

አበበ፦ ወንጌልማ የመስቀሉ ስራ ነው፥ በመስቀል ላይ ስለኛ ሀጢያት ሲል ደሙን አፍስሶ መሞቱ ነው፥ ወንጌል ማለት በኢየሱስ የመስቀል ስራ አምኖና ጌታን ተቀብሎ ከገሀነም እሳት ማምለጥና መንግስተ ሰማይ መግባት ነው። ወንጌል ኢየሱስ ነው!

ከድጃ፦ እኔ ቅዱስ ቁርዐናችን ላይ ኢሳ (ኢየሱስ) አረገ እንጂ ሞተ የሚል አላነበብኩም። ለማንኛውም መውረጃዬ ደርሷል ደና ሁን (ብላው ከባቡሩ ወረደች) 
*          *           *
ያበበን እና የከድጃን ንግግር በውል ካጤንኩ በኃላ፣ በመጠኑም ቢሆን የከድጃን መፅሐፍ ቅዱስ አንባቢነት እና በረጋ መንፈስ ውይይት መምረጧን አድንቄ፤ እንዲሁም አበበ ምንም እንኳን የሚያምንበን ሀቅ በቅጡ አለማወቁና ተገቢ መልስ መስጠት አለመቻሉ ቢያሳዝነኝም፥ ዳሩ ግን ስለሚያቀው ነገር ለመናገር ያለውን ድፍረት አድንቄ ሳበቃ ስለ ወንጌል የተናገረውን ትልቅ እና መሰረታዊ ግድፈት ሳላርመው አልወርድም ብዬ እንዲህ ስል ወንጌልን "ለወንጌላዊው" ሰበኩለት። 

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እና በአምሳሉ ሲፈጥረው የእግዚአብሔርን ሰማያዊ መንግስት ምድር ላይ በማስረፅ ምድርን እና ሞላዋን እንዲገዛ (Dominion)  ነበር ያዘዘው፤ ነገር ግን አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር እንዳትበሉ ብሎ ካዘዛቸው ፍሬ በመብላት ትዕዛዙን በመጣሳቸው ምክንያት ከገነት ተባረው ምድርን በሰማያዊ መንግስት የመግዛት ሀይላቸውን እና ስልጣናቸውን አጡ። ከዛም ብዙ ትውልድ ካለፈ በኃላ በነብያቶች እንደተነገረው ጊዜው ሲደርስ፣ ከድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ በነ አዳምና ሔዋን አለመታዘዝ የሰው ዘር ያጣውን የእግዚአብሔር መንግስት ይዞልን መጣ። በነብዩ ኢሳያስ እንደተነገረው "ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም (መንግስት) በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።"
የእግዚአብሔር መንፈስ ከነ አዳም ውድቀት ጀምሮ በሰው ልጆች ላይ እየወረደ በተለያዩ ወቅቶች ስራ መስራትን አላቆመም ነበር ነገር ግን ከእግዚአብሔር መንግስት ውጪ ነበር፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ሁለተኛው አዳም ከሐጢያት ነፃ ሆኖ ነፍሱን ቤዛ አድርጐ የሰውን ዘር ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ ድሮ አጠነው የእግዚያብሔር መንግስት ሊያወርሰን የመጣው። ለዛ ነው ይሄ ወንጌል የምስራች የሚባለው። ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ መስቀል አይደለም።
ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ የኢየሱስ ደም አይደለም።
ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ ዳግም መወለድ አይደለም። ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ ደህንነት አይደለም።
ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ ሞትና ትንሳዔ አይደለም።
ወንጌል የእግዚአብሔር መንግስት እንጂ ኢየሱስ አይደለም።

አበበ፦ ምን? ወንጌል ኢየሱስ አይደለም ነው ያልከው? 

እኔ፦ አንተ አልህ! (በኪሴ የያዝኳትን መፅሐፍ ቅዱሴን እየመዘዝኩ) እስቲ ከዚህ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ሰው በተሰበሰበበት ስለ መስቀሉ፣ ደሙ፣ ደህንነት፣ ዳግም ውልደት ወይም ስለራሱ የሰበከበትን ክፍል አሳየኝ አልኩት።  (እኔ አበበ ላይ አበበ መፅሐፍ ቅዱሱ ላይ ትንሽ ስናፈጥ ከቆየን በኃላ) 
ማቴዎስ 4:17ን ገለጥኩና "የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።"
ከሚለው ተነስቼ እስከ ሐዋርያት ስራ 1:3 ድረስ ያለውን የኢየሱስን ስብከት አሳየሁት፤ "ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።"

ወንጌል የኢየሱስ ሞትና ትንሳዔ ነው ካልክ ነገር ግን ኢየሱስ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሞቱ ለማንም እንዳይናገሩ ካስጠነቀቃቸው ታዲያ የቱ ጋር ኢየሱስ ወንጌል የሰበከው? 
ወንጌል ዳግም ስለመወለድ እና መንግስተ ሰማይ ስለመግባት ከሆነ፣ ታዲያ እንዴት ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ በለሊት በግሉ ሊያናግረው ከመጣው ኒቆዲሞስ ጋር ብቻ ስለ ዳግም መወለድ አወራ? የቱ ጋር ነው ኢየሱስ ስለ ዳግም ውልደት ለህዝቡ ሲሰብክ ያየኀው?
(የአበበ ፊት እንደ ኢትዮጵያ ኔትወርክ ቢዚ እና ዲዚ ሲሆንብኝ ከዚህ በላይ ከጨመርኩበት ጥሩ አይመጣም ብዬ የከድጃን ስልክ ቁጥር ተቀብዬው ከባቡሩ ወረድኩ)

በመንገድ ላይ እያዘገምኩ  ስለ ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን እና ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሳሰላስል ድንገት ያያቴ አባባል ትውስ አለኝ። "እሳት ቢበርደው በምን ይሞቃል? ገመድ ቢያብድ በምን ይታሰራል?"












Sunday, 3 July 2016

የፀሎት ቤት Vs የምናምን ቤት





ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ከሀገር ቤት ደውላ የእግዚአብሔርን ቃል በህብረት የምቆርስበት ሁነኛ የፀሎት ቤት ጠቁመኝ ስትለኝ እኔም ብዙ ካወጣሁ ካወረድኩ በኃላ እከሌ ወደሚባለው የፀሎት ቤት እንድትሄድ መከርኳት ("ነብይ" ተብየው መከራዋን አሳያት እንጂ) ፕሮግራሙ ካለቀ በኃላ የነገረችኝን ሳስበው፣ እራሴኑ መልሼ እውነት ግን ወደ ፀሎት ቤት ነው ወይስ ወደ ጠንቋይ ቤት ነው የመራኃት እያልኩ ሳሰላስል፤ ጌታችን ጅራፍ ሲገምድ ባይነ ህሊናዬ ድቅን አለብኝ። 
ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተፅፏል እናንተ ግን.....

ነገሩ መች በወንበዴዎች ቤት ቀረና፤ አሁን ደሞ መልኩን አሻሽሎ አንድ በጠንቋይ ቤት፣ በንግድ ቤት፣ ሲያሻው በዳንኪራ ቤት መገለጥ ከጀመረ ሰነባበተ።

የፀሎት ቤት Vs የጠንቋይ ቤት

ያቺ ከላይ የጠቀስኳት ወዳጄ እንዳለችኝ ከሆነ፣ ሰውየው መድረክ ላይ እየሸለለ እንዲህ ማለት ጀመረ፣ አንድ ሴት አለሽ ባሰሪዎችሽ ውጊያ የበዛብሽ፣ እጅሽን አውጪ፤ የኔ ነገር እስከመቼ እያልሽ ቀን ከሌት የምታነቢ፣ (እስቲ አሁን ይታያችሁ እምባ sale ላይ በወጣበት ሀገር ሰው በቀን ሦስቴ በልቶ ሳይሆን አልቅሶ በሚያድርበት ሀገር እንዲህ ብሎ መልዕክት፤ ምናልባት ሰውየው ጀማሪ "ነብይ" ሳይሆን አይቀርም) ለምልክት ይሆን ዘንድ ቀይ ቀለም ፓንት ነው የለበሽው አለ። (ይሄኔ ነው እንግዲህ ጉባዔው ውስጥ የታደመው ወንድ ሁሉ የልጅቱን ፓንት እያሰበ ወደ ሌላ አለም የገባው። ግማሹ በልቡ፣ ምነው ግን ይሄ አይቶ የተመኘ.....ምናምን የሚለው ቃል ባይኖርና ነብዩ የጀመረልንን Erotic ፊልም ብንጨርስበት ይላል) በመቀጠል ያ ውቃቢ የራቀው ሰውዬ፣ የኔ እህት፣ ስልክ ቁጥርሽን በራዕይ እያየሁት ነው አለና "ከነብይነት" ወደ ቴሌ ሰራተኛነት በመቀየር 0911666....ማለት ሲጀምር፥ ያቺ ሴትዮ ቀዩን ሳይሆን አረንጓዴው ፓንቷ እስኪታይ ድረስ ወለሉ ላይ መንፈራገጥ ጀመረች። (I think "ነብዩ" Colour blind ሳይሆን አይቀርም) ሰውየው ሞቅ አለውና፥ ዛሬ የምታያቸውን ግብፃውያን፥ ለዘላለም አታያቸውም! ሲል፣ ጉባዔው በጩኀት ተናጋ። (ወይ ጉድ! ሰው ይሞታል ሲባል እንዲህ ጮቤ መርገጥ) 

እረ የታለ ያ የየሱስ ጅራፍ?

ከዛማ ምኑ ይወራል? ሰውየው ከግል ካድሬዎቹ የክት ልብስ ላይ ላቡን እየጠረገ፤ ጉባዔውን ባንድ እግሩ ያቆመው ጀመር። 
ሦስት አግብቶ የፈታውን፥ ጌታ በድንቅ እድርሀለሁ ይልሀል ሲለው፤ ሊሞት አንድ ሐሙስ የቀረውን፥ ገና እድሜ አጠግብሀለሁ ብሎ ሲመርቀው፤ በየካፌው ማኪያቶ ሲልጥ የሚውለውን፥ ጌታ ገና ምኑን አይተህ አለምን አዞርሀለሁ ይልሀል ሲለው፤ ኑሮ ከብዷት የፊት ማድያቷ ለሚያሳብቅባት ምስኪን፥ ዘንዶው ተወጋ ሲላት፥ እሷም በምርቃና ብዛት በያዘችው ዣንጥላ ሰው መውጋት ስትጀምር፤ 
ግማሹ፥ ሚሊየነር ትሆናለህ ሲባል፤ እኩሌታው፥ በቤት ላይ ቤት በህንፃ ላይ ህንፃ ትገነባለህ እየተባለ፥ ቤቱን እኛ ሰፈር ያለውን የአዋቂ ቤት አስመሰለው።

የፀሎት ቤት Vs የዳንኪራ ቤት

የኢየሱስን አኗኗር አይቶ የዘመናችንን ቤተክርስቲያን ላስተዋለ፣ ዘንድሮ በፀሎት ቤቱ ውስጥ የሚካሄደው ፀሎት እና ትምህርት ሳይሆን መዝሙር ግርፍ እኔ ፈንጠዝያ ብቻ ነው። ኢየሱስ፦ ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ሲል፥ እኛ ደግሞ በፊናችን፥ ቤቱን የዳንኪራ ቤት አርገነው ቁጭ። በጣም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፥ ኢየሱስ ብዙ ጊዜውን የተጠጠቀመው ለፀሎት፥ ለስብከት እና ለትምህርት ነበር፤ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደዘመረ ተፅፎልናል። (ማቴዎስ 26:30ን ተመልከቱ) እሱ አንዴ ዘምሮ ሺህ ጊዜ ፀለየ፤ እኛ ሺህ ጊዜ እየዘመርን፥ አንዴ እየፀለይን ቤቱን የዳንስ ቤት አርገነው የኢየሱስ ተከታዮች ነን ስንል ግን አናፍርም? ደቀ መዝሙር ማለት እኮ መምህሩን እየተከተለ የሚደቃ ማለት እንጂ የመምህሩን ማዕረግ የሚደቃ ማለት አይደለም። እስቲ በሚመጣው እሁድ ወደየ ፀሎት ቤታችሁ ስትሄዱ ልብ ብላችሁ ለፀሎት እና ለመዝሙር የሚመጣውን ሰው ተመልከቱ። ከዚያም ፀሎት እና መዝሙር ምን ያክል የሰዓት ድርሻ እንደሚሰጣቸው ተመልከቱ። ምን እሱ ብቻ፥ መዝሙር ለመምራት ከሌላ አህጉር ድረስ ሰው እናስመጣለን ፀሎት ለመምራት ግን አለሙ ካልተመቸው ከበደን እንዲመራ እናረገዋለን። ምክንያቱም ቤቱ የመዝሙር እንጂ የፀሎት ከሆነ ቆይቷላ። ለነገሩ አልተኛም ሌሊቱን ቁጭ ብዬ አነጋለሁ የሚሉ ዘማሪዎች በሞሉበት ሀገር ኢየሱስ ሌሊቱን በሙሉ በመዝሙር ሳይሆን በፀሎት እንደሚያነጋው እንዴት እንወቅ? "እርሟን ብታፈላ ስኒ ሙሉ አተላ" አለ አጐቴ። ደሞ እኮ እንዲህ እንቅልፍ አጥተን ሰራነው የሚሉት መዝሙር ቅጠል ቅጠል የሚልና ስሜትን አልፎ መንፈስን የሚነካ አለመሆኑ ነው። አጠጣኅኝ፥ አጐረስከኝ ከሚለው የምግብ ቤት መዝሙራቸው ያለፈውም ቢሆን ነፍሱን ይማርና ከመዝመረ ዳዊት የተቀዳ ነው። ዛሬ መዝሙረ ዳዊት በህይወት ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁሉ እንደ አሸን የፈላ ዘማሪ በቅጂ ወንጀል እስር ቤት እንጂ እግዚአብሔር ቤት አይገኝም ነበር። (ታዲያ ይሄን ስል ሁሉንም ዘማሪዎች እየወረፍኩ አይደለም። ለምሳሌነት ደረጀ ከበደን ማንሳት ከበቂም በላይ ነው)

የፀሎት ቤት Vs የንግድ ቤት

አንድ ወዳጄ ስለ ስራ ሁኔታው ስጠይቀው ባክህ ዘንድሮ ስራ ቀዝቅዟል፣ ዝምብዬ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪውን ብከፍት ነው የሚያዋጣኝ ይለኛል፤ እኔ ደሞ ቀበል አድርጌ፣ ምን? ቦቆሎ ልትዘራ አሰብክ እንዴ? ስለው፥ ምን በወጣኝ እና ነው ከጭቃ ጋር የምታገል? 20 ሰው ሰብስቤ፣ ኪሳችሁ ኪሴ ነው የሚል international church ልከፍት ነው እንጂ አለኝ። ያኔ ነው በየመድረኩ ላይ የሚፈፀመውን ግብይት ማሰላሰል የጀመርኩት፤ የግዜር ቃል ያላግባብ እየተጠቀሰ የኔ ቢጤውን ማራቆት ከተለመደ ቆየ። ጌታችን በሉቃስ 6:38 ላይ የተናገረውን "ስጡ ይሰጣችኋል" የሚለውን ቃል በማጣመምና ህዝቡን በማስገበር ፓስተሩ የህንፃውን መስታወት ያስገጥማል። ትንሽ ከፍ ብላችሁ ስታነቡት ግን ጌታችን እያለ የነበረው ለጠላቶቻችን ሩኅሩኆች ሁኑ ነበር፤ ስጡ ይሰጣችኋል የተባለው ለጠላቶቻችን እንጂ ለፓስተሮቻችን ወይም ለነብያቶቻችን አይደለም። አስራት፥ መባ፥ ስጦታ፥ ዘር እያሉ ስሙን እያቆላመጡ ህዝቡን ያስመነዝሩታል። መች በዚህ አቆሙና፣ በዛው በነካ እጃቸው "ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው" እያሉ እነሱ የራሳቸው መኪና ይሸምታሉ፤ ጳውሎስ ግን በሐዋርያት ስራ 20:35 ላይ የሚያወራው ለድሆች ስለመስጠት እንጂ ለዘማሪዎች አይደለም። ዛሬ ያንተ በስራ መባከን እና ህይወት መድከም ግድ የሚለው የለም ይልቅ አንተ እንኳን ባትመጣ አስራትን ላከው ይልሀል እንጂ። ቤቱን ከፀሎት ቤትነት ወደ ንግድ ቤትነት መቀየር ይሏል እንዲህ ነው። 
*                           *                             *

የእግዚአብሔር ቤት ተጠሪነትዋ ለእግዚአብሔር መንግስት የሆነች ተጠርተው ለወጡ የእግዚአብሔር እንደራሴ (ambassador) የስልጠና እና የፀሎት ማዕከልእንጂ የኛን ሐይማኖት የምናስፋፋባት ቤት አይደለችም። 
ጆሮ ያለው ይስማ።