Friday, 13 May 2016

ሰካራሙ ሰይጣን


ያለወትሮዬ ከእትዬ ቀለሟ ጠላ ቤት ወረድ ብሎ ባለው ጥባብቅ መንገድ ዳር ቀበሮ የማሰው ጉድጓድ ውስጥ ለንግላል የተፈነገለ አይኑ እንደ በርበሬ የቀላ መልከ መልካም ጐልማሳ በማየቴ ልረዳው ዝቅ ስል ከብብቱ አጠገብ ሉሲፈር የሚል መታወቂያ አስተዋልሁ። ድንገት የጋዜጠኝነት ሙያዬ ሲታወሰኝ ልረዳው የነበረውን መናጢ ስካሩን አሳብቤ ላዋርደው ከጀልኩና ለጥያቄ ቢተባበረኝ የዶሮ አይን የመሰለ አንድ ሙሉ ማንቆርቆሪያ ጠላ ከነ አሹቁ ጀቫ እንደምለው ስነግረው በመስማማቱ ወደ ጥያቄዬ ገባኁ።

እኔ፦ ግን ምን ሆነህ ነው እንዲህ ጥምብዝ እስክትል ድረስ የጠጣኀው?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ (እጁን በቁጣ ወደላይ እያወናጨፈ) እረ ተወኝማ ደና የረሳሁትን ብስጭቴን አታንሳብኝ።

እኔ፦ ማነው ደሞ ዲሞክራሲ ባለበት ሐገር አንተን የሚያበሳጭህ? 

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ስማቸውን ቄስ ይጥራውና እነዚህ ጴንጤዎች ናቸዋ!

እኔ፦ (እ... አልኩኝ ነገር በገባው ቋንቋ) በጣም እየገሰፁህ አላሰራህ አሉህ አይደል? "ላይችል አይሰጥ" አለ ኢዮብ፤ በል እንግዲህ ቻል አርገው።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ አይይ... "ፅድቁ ቀርቶብህ በቅጡ በኮነነህ!" የምን መገሰፅ አመጣህ? አስር እጅ እሱ ይሻለኝ ነበር። አለ (ቁጭት በሞላበት ድምፅ)

እኔ፦ ታዲያ ምን አረጉኝ ነው የምትለው? ምን ይለጉምሀል አትናገርም?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ (በጃኬቱ የውስጥ ኪስ የቀረቀረውን ሃይላንድ ሙሉ ጠላ ከፍቶ ከተጐነጨ በኃላ ጉሮሮውን አፅድቶ ገባበት) እኔን አሁን ምርር ያረገኝ ያ ቤት የማይመታው ጩኅታቸው ሳይሆን በሆነ ባልሆነው በኔ የሚያሳብቡት ነገር ነው። አዳሜ ወሬዋን እየቀደደች ሽንኩርቷ ባረረ ቁጥር እኔ መወቀስ አለብኝ? ነው ወይስ ሌባው ሊያርድ ይመጣል የሚለውን ሽንኩርት ሊያሳርር ይመጣል ብላችሁ ነው ምታነቡት? ለነገሩ እሱም ቢሆን ስለ ሐሰተኛ እረኞች እንጂ ስለ እኔ አልተፃፈም።

እኔ፦ አንተ ደሞ ጀመረህ እንግዲህ፣ እህህ ብሎ የሚሰማህ ካገኘህ እኮ ጆሮን በውሸት ደም በደም ነው 'ምታረገው።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ጊዮርጊስን! እውነቴን ነው። ትዝ ይልሀል እማሆይ ገዳም ውስጥ ምን እንደሰሩ?

እኔ፦ አንተ ደሞ እንደ መለስ ዜናዊ ዙሪያ ጥምጥም መዞር ስትወድ፣ ምን ነበር ግን የሰሩት?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ያለልማዳቸው የፍልሰታ ፆም ጊዜ እንቁላል ጥብስ ያምራቸውና ምን እንደሚያረጉ ጭንቅ ጥብብ ይላቸዋል፣ ከዛ ደበቅ ብለው ጧፋቸውን ለኩሰው እንቁላሏን መጥበስ እንደጀመሩ ድንገት የገዳሙ አስተዳዳሪ እጅ ከፍንጅ ያዟቸውና፥ ምነው እማሆይ ምን ነካዎት? በፆሙ እንቁላል ጥብስ? ሲሏቸው እማሆይ ቀበል አርገው እንደው ይቅር ይበሉኝ ሰይጣን አስቶኝ ነው እንጂኮ እኔማ ለቁላልም አላርጅክ ነኝ። አይሉም መሰለህ? ከዛ ውሸታቸው በጣም ስላናደደኝ ወዲያው በስጋ ተገልጬ፥ ምነው እማሆይ፥ ለምን ይዋሻል ግን? እኔ ራሴ እንደዚህ አይነት የእንቁላል አጠባበስ ዘዴ ከርስዎ አይደል እንዴ ዛሬ ያየሁት? መቼ ነው ግን ሰዎች ስትባሉ ለጥፋታችሁ ሀላፊነት የምትወስዱት? ብዬ እማሆይን አስገብቼላቸው በዛው እልም አልኩ።

እኔ፦ ታዲያ ከያንዳንዱ ሀጢያት ጀርባ አንተ ከሌለህ ማን አለ? አንተ አይደለህ እንዴ ከሄዋን ጀምረህ ሰውን ሁሉ በዚህ መንታ ምላስህ እየዋሸህ ጉድ የሰራኀው? ታዲያ ብርቅ ነው እኛ ባንተ ባናመካኝ? ነው ወይስ ሌላ የማናቀው ሰይጣን አለ? 

ሰካራሙ ሰይጣን፦ "ነገርን ነገር ያመጣዋ" አለ ዮሴፍ። ሌላ ሰይጣን ስትል ምን ትዝ አለኝ መሰለህ? ጥያቄዬን በጥያቄ መለስከው አትበለኝ እንጂ፤ ለመሆኑ የዛሬን አያርገውና ያኔ እኔ መልዐክ እያለሁ የትኛው ሰይጣን አስቶኝ ነው ከብርሀን መልዐክነት ወደ ጨለማ መልዐክነት የተቀየርኩት? የትኛው ሰይጣን ነው እኔ ሰይጣንን ዋሽቶ ያሳተኝ? እንግዲህ እኔ የሀሰት አባት ከተባልኩ፣ አባት ማለት ደሞ ምንጭ ማለት ከሆነ፣ ታዲያ እኔን የተፈታተነኝና ያሳተኝ ማን ነበር?

እኔ፦ (መልሱ ከፀጉሬ ውስጥ ይገኝ ይመስል ራሴን እያከኩ እእእ.... ማለት ስጀምር)

ሰካራሙ ሰይጣን፦ (የጠጣውን ጠላ እያገሳ ከሳቀብኝ በኃላ) ምነው እውነቱን ለመናገር ፈራህሳ? ምነው አንተ ነህ ማለት ፈራህ? ምነው ከጀርባዬ ሌላ ሰይጣን አለመኖሩ አበሳጨህ? ገብቶኛል። በሆነ ባልሆነው በሰይጣን ማሳበብ በለመደ ህብረተሰብ ውስጥ አድገህ ብትፈራ አይገርመኝም። ወገቡ ይቆረጥ፣ አንጀቱ ይዘርገፍ እየተባለ ሰይጣን በሚሰደብበት ቤተክርስትያን ውስጥ አድገህ ለነገሩ ካንተ ምን እጠብቃለሁ።

እኔ፦ ታዲያ ማን ነበር ላንተ መሳት መንስዔው እያልከኝ ነው?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ፈቃዴ

እኔ፦ የምን ፈቃድ አመጣህ ደሞ?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ አየህ ነፍሳችን ሦስት ነገሮችን ይዛለች። እነሱም፦ ስሜት፥ እውቀት እና ፈቃድ ናቸው። እኔ መልዐክ በነበርኩበት ወቅት በልቤ እንድታበይ እና እንደ እግዚአብሔር ለመሆን የከጀልኩት በገዛ ፈቃዴ ተስቤ ነው እንጂ ከኔ በፊት ሌላ ሰይጣን ኖሮ አይደለም። ለሰው የገዛ ፈቃዱ ለለውድቀቱም ሆነ ለመቆሙ ምን ያክል ሀይል እንዳለው የተረዳችሁ አይመስለኝም። በዚያ ምድረ በዳ ላይ ኢየሱስን አርባ ቀን ስፈትነው በፈቃዱ እምቢ ብሎ ፈተናውን አልፎ ያሳያችሁ እኮ ከሱ ትምህርት ወስዳችሁ በህይወታችሁ እንድትኖሩበት እንጂ ጊዜ ተርፎት እኮ አይደለም ከኔ ጋር ያሳለፈው። (Your free will is more powerful than the devil) ታዲያ ከዚህ ትምህርት አትወስድም? 

እኔ፦ የምን ትምህርት? 

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ከመልዐክት አለቅነት አንስቶ ሰይጣን እስከማድረስ የዳረገኝ የራሴው ፈቃድ መሆኑ ነዋ። ይሄን ለሚያህል ውድቀት ፈቃዳችን ሀይል ካለው ታዲያ ምን ስለሆናችሁ ነው በሆነ ባልሆነው በኔ ምታሳብቡት? ለነገሩ ካባታችሁ አዳም ያመጣችሁት ነው። ታውቃለህ ግን ሁሌ በኔ ባሳበባችሁ ቁጥር፣ ለገዛ ስንፍናችሁ መፍትሄ ማምጣት እንደማትችሉ? እያንዳንድሽ ስኳር እና ዘይት እንደ ኦክስጅን ስትልፊ ኖረሽ በኃላ ስትታመሚ ሰይጣን ተዋጋኝ ትያለሽ ወይም ደሞ ላየሀት ሴት ሁሉ ጥብስ እየጋበዝክ ገንዘብህን የትም ስትዘራ ኖረህ በኃላ የቤት አከራይህን ስታይ ሰይጣን ገንዘቤን ሰለቨኝ እያልክ መራገም፣ ምን ይሄ ብቻ፥ ማታ ፊልምሽን ስትለሸልሺ አምሽተሽ በእንቅልፍ ልብሽ ስራ ገብተሽ ግማሹን ቀን እንቅልፍሽን ዋሽ ሩም እየጨረሽ ካለቃሽ ጋር ስትጋጪ ሰንብተሽ ያቺ መከረኛ እሁድ ስትደርስ፥ እባካችሁ ወገኖቼ በአለቃዬ የሚጠቀም የቤልዛቤልን መንፈስ ተቃወሙልኝ እያልሽ ከኔ ጋር ጦርነት መግጠም። እረ የናንተ ጉድ ቢወራ መች ያልቃል! (አለ ጠላውን እየተጐነጨ)

እኔ፦ (በዚህ ስካር ሙድ ላይ እንዳለ ብዙ መረጃ ልሰብስብ ብዬ ቀጥል የሚል ምልክት በጄ ሰጠሁት)

ሰካራሙ ሰይጣን፦ "መጋደላችን ከደምና ከስጋ ጋር አይደለም" ተብሎ ቁልጭ ብሎ ተፅፎላችሁ እንዴት ብትደነዝዙ ነው ግን ራሱ ይጨፍለቅ፣ ጨጓራው ይዘርገፍ፣ አይኑ ይወጋ፣እግሩ ይሰበር ምናምን እያላችሁ ሆረር ፊልም የምትሰሩት? ሰሞኑን ፖስተር ተብየው ምን እንደነካው አላቅም ጉባዬውን ባንድ እግሩ አቁሞ የሰይጣንን ጭንቅላት ከፍተን ሰልፈሪክ አሲድ እንጨምርበታለን አይልም መሰለህ? ማንም የክሬዲት ካርድ እዳ ናላውን ሲያዞረው በእምነትን እያስመሰለ የንዴቱ መወጫ ያርገኝ?

እኔ፦ መችም ሰው መንፈስ መሆንህን እያወቀ ጭንቅላት ምናምን ሲል በተምሳሌት ስለ አስተሳሰብህ እያወራ ነው እንጂ በቀጥታ ስለ ጭንቅላትህ እያወራ ነው ብዬ አላስብም።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ እና ታዲያ ወገቡ ይወጋ ስትል ምኔን ለመግለፅ ይሆን? እንደው ችክ ስትል ነውጂ አሁን እውነቱ ጠፍቶህ ነው? እስት ጌታችሁ ኢየሱስን በዚያ ጭው ባለ ምድረበዳ ባልበላ አንጀቱ ስፈትነው ምን እያለ እንደተቃወመኝ አስታውስ። የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ሳለ፥ እስኪ የግዜር ልጅ ከሆንክ ብዬ የጀመርኩት ያለነገር ይመስልሀል? አንተ ብትሆን ኖሮ ይሄኔ እንዴት ልጅነቴ ተደፈረ ብለህ ያገሩን ሁሉ ድንጋይ ሰብስበህ ዳቦ ቤት ትከፍት ነበር። ምን እሱ ብቻ እስቲ ከዚህ ወደታች ራስህን ወርውር ስለው፥ ምን እንዳለኝ ትዝ አይልህም? አንተ ብትሆን ኖሮ ትንሽ በልሳን ሸልለህ ስታበቃ ቅጥሩን ያዘልለኛል ብለህ ባፍጢምህ ትደፋ ነበር። እስቲ ተመልከት ኢየሱስ እንዴት አርጐ እንደቃወመኝ፥ የትኛው ቦታ ነው አንጐልህ ይበጥበጥ፥ ጨጓራህ ይቃጠል ምናምን እያለ የገሰፀኝ? እንዲህ ተብሎ ተፅፏል እያላችሁ ተቃወሙ ተባላችሁ እናንተ ግን የጦርነትና የጠብ ነገር መችም ያምራችኋል ነጋ ጠባ ከኔ ጋር መቧቀስ። ለመሆኑ ዲያብሎስን ተቃወሙት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶሀል? 

እኔ፦ እያዳመጥኩህ ነው ቀጥል...

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ሲጀመር ተቃዋሚ ማለት Opposition በሚለው ስታየው ከተቃዋሚ ወገን የሚመጣውን ማንኛውንም አይነት ሀሳብ የምትቃወመው ሀሳቡን ባለመፈፀም እንጂ ጐራዴ ይዘህ ስለፎከርክ አይደለም። ስለዚህ መቃወም በኑሮ እንጂ በወሬ አይደለም። ሲያስፈልግ እንደ ዮሴፍ ሮጦ ማምለጥ እንጂ የዝሙት መንፈስ ውደቅ እያሉ አብሮ መውደቅ አይደለም። ለነገሩ በጦርነት የኖረች ሀገር ውስጥ አድጋችሁ፤ መሳደብና መጣላት እንደ ሱስ ቢያምራችሁ አይገርመኝም። እኔ ምልህ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚጠላኝ ይመስልሀል?

እኔ፦ ድብን አርጐ ነዋ!

ሰካራሙ ሰይጣን፦ Dude! እግዚአብሔር ግን ኢትዮጲያዊ ነው አይደል የሚመስልህ? እግዚአብሔር የሚጠላው ሀጢያትን ነው። እኔም ብሆን እኮ እንደናተው ሀጢያት የሰራሁት፤ ምን የተለየ ነገር አለ? ግን ዋጋዬን አግኝቻለሁ። የኢዮብን ታሪክ ተወውና እስኪ በቅርቡ እንኳን ኢየሱስ ሊለቀል ገደማ ጴጥሮስን ምን እንዳለው ትዝ ይልሀል? 

እኔ፦ አይለኝም።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ እኔዴት ትዝ ይልሀል ለነገሩ፤ መፅሐፉን ካነበብክ ፊልሙን እና መዝሙሩን ማን ያይልሀል? ይሄኔ የሆሊውድ ተዋንያኖችን ስም ብጠይቅህ፣ አይደለም ስማቸውን ከነጋ ስንቴ እንዳስነጠሱ ትነግረኛለህ፣ ግን የአስራ ሁለቱን ሐዋርያት ስም ብጠይቅህ ላበትህ ይመጣል። ይልቅ እሱን ተወውና ወደ ጴጥሮስ ታሪክ እንመለስ፣ ምን መሰለህ ኢየሱስ ያለው፣ እነሆ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስላንተ ፀለይኩልህ፤
እናንተ ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ሽምጥጥ አርጐ መካዱ ነው ሚገርማችሁ፤ እንደ ስንዴ እንዳበጥረው ቢፈቀድልኝ ኖሮ ጴጥሮስን ራሱን እንደ ዶሮ ነበር የማስጮኀው። ለማንኛውም ይሄን ሀሳብ ያመጣውልህ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የነበረኝን የይለፍ ፈቃድ Access ላሳይህ ነው፤ ትዝ ይልሀል እባክህ ወደ እሪያዎቹ አስገባን ብለን ስንለምነው፣ እሺ ብሎ ሲያስገባን? ስማ እኔ ለማንነቴ የምጨነቅ አይምሰልህ፣ "የትም ፍጭው ነው ነገሩ" ዋናው ነገር ሰው መሳቱ ነው ለኔ። 

እኔ፦ መፅሐፉን ግን ደህና አርገህ ይዘኀዋል፣ ለመሆኑ የማትወደው ጥቅስ የትኛው ነው?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ እናንተ እንደሆናችሁ ለሁ ነገር ካልተጠቀሰላችሁ አያስችላችሁም፣ ስለዚህ እኔም እየጠቀስኩ ማሳቱን ተያይዤዋለሁ። ሞኝ መሰልኩህ ከቁርዐን ብጠቅስ ማን ይሰማኛል? ትዝ ካለህ ገነት ውስጥም እግዚአብሔር ከተናገረው ጠቀስ አርጌ ውሸቷንም ጨማምሬ ነው ማሳት የጀመርኩት። ኢየሱስን ቢሆን እየጠቀስኩ አይደል ላጭበረብረው የሞከርኩት። ለማንኛውም ወደ ጥያቄህ ስመለስ ሆሴዕ 4:6 አይመቸኝም።

እኔ፦ ለምን?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩህ፣ ነፍሳችሁ ስሜታችሁን፥ እውቀታችሁን እና ፈቃዳችሁን ስለያዘች፣ የፈለገ ነገር ቢሰማህ ፈቃድህን የምትሰጠው እንደ እውቀትህ መጠን ነው። እግዚአብሔርም ሆነ እኔ የምንሰራው በፈቃዳችሁ ስለሆነ፣ ጦርነቱም ያለው እዚያ ላይ ነው። የድንቁርና እና እውቀት በእብራይስጥ ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ? ድንቁርና ማለት ጨለማ ሲሆን እውቀት ማለት ደሞ ብርሀን ማለት ነው። እኔ ደሞ እንደምታቀው የጨለማው አለም ገዚ ነኝ። ያ ማለት ማታ ማታ ብቻ ነው የምሰራው ማለት ሳይሆን፣ ህይወታችሁን ለማጥፋት የምጠቀመው ድንቁርናችሁን ነው ማለት ነው። ድንቁርናህ በጨመረ ቁጥር የኔም ተፅዕኖ በሂወትህ ላይ ይጨምራል ማለት ነው። ለዛ ነው ያንን ጥቅስ የማልወደው፣ ምክንያቱም ሰው ሁሉ ባኖ የነቃና እውነቱን ያወቀ ቀን ብቻዬን መቅረቴ ነው እያልኩ ስለምፈራ ነው። ግን እድሜ ለናንተ ከትምህርት ይልቅ መዝሙር ስለምትወዱና ስለምታዘወትሩ ብዙም አያሰጋኝም። በቀደም ለስራ ጉዳይ ወደ አንድ የእሁድ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሄጄ ለሙዚቃ መሳሪያ መጫወቻ፣ ለኳየር አልባሳት፣ ድምፅ ማጉያ ስፒከር ምናምን መግዢያ ያወጡትን ብር አይቼ ተገርሜ እስቲ ደሞ ላይብረሪያቸውን ልይ ብዬ ብፈልግ ከየት ይምጣ? ወይ ላይብረሪ እቴ! ከዛ ሳስበው አሁን ለነዚህ ምን ጊዜዬን አቃጠለኝ ብዬ ጥያቸው ወጣሁ።

እኔ፦ እሱማ ተሰብስበው ጌታን እያከበሩ ነው።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ ሃሃሃ... እያከበሩ አልከኝ? በዮሐንስ ወንጌል 17:4 ላይ ኢየሱስ ምን እንዳለ ታውቃለህ? እኔ ላደርገው የሰጠኀኝን ስራ ፈፅሜ በምድር አከበርኩህ። ነው ያለው። እግዚያብሔርን ማክበር ጭብጨባና በእልልታ ሳይሆን የምትኖርበትን ዓላማ እንደተባልከው በመፈፀም ነው የምታከብረው። ስለዚህ በመዝሙር ሳይሆን በኑሮ ነው። ለነገሩ የተሰጣችሁን ስራ እንኳን በቅጡ የምታውቁት ስንቶቻችሁ ናችሁ?  ደሞ እንዲህ ድንቁርና እየተዳፋችሁ እኔ ላይ እንዳንበሳ ስትሸልሉ እኮ አንዳንዴ ትዕግስቴ አልቆ እንዳስቄዋ ልጆች በቦክስ ባናፍጣችሁ ደስ ይለኛል። አለ በንዴት የቀረውን ጠላ እየጨለጠ

እኔ፦ እሱ ነገር አለቀብህ አይደል? አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅህና እገዛልሀለሁ፤ ለመሆኑ ለጴንጤዎች የመጨረሻ የምትለው ነገር አለህ?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ አይ ያንተ ነገር፣ ስንቱን አንስቼ ስንቱን እጨርሰዋለሁ? አለና ትንሽ አሰብ አርጐ ሲያበቃ እንዲህ አለኝ ድንቁርናውና ሌላው ኮተታችሁ እንዳለ ሆኖ፣ አንድነት የሚባል ነገር አልፈጠረባችሁም። ይሄ ጦሳችሁ ደሞ ከናንተም በህብረተሰባችሁ እና በሀገር አፍ ደረጃም ተንሰራፍቷል። አንድነት ሀይል ነው እያላችሁ ከመለፈፍ ባለፈ ሀይሉ የቱ ጋር እንዳለና እንዴት እንደሆነ የገባችሁ አይመስለኝም። 

እኔ፦ እስቲ ሀይሉ እንዴት እንደሆነ አሳየኝ።

ሰካራሙ ሰይጣን፦ (እንደምንም ብሎ ባለ በሌለ ሀይሉ እየተጣጣረ ተጠጋኝና) ከየት መጣ ሳልለው ከመንጋጭላዬ ስር በቡጢ ሲለኝ ሰማይ ምድሩ ተደበላልቆብኝ በኃላዬ ተዘረርኩኝና ትንሽ መለስ ሲልልኝ እንዳልኝ መሬቱን ባንድ መዳፌ፣ መንጋጭላዬን ባንድ መዳፌ ይዤ፥ እንዴ! ምን አረኩህ? ምን የሚያበሳጭ ነገር ተናግሬህ ነው እንደዚህ የመታኀኝ?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ እኔ ምን አረኩህ? ራስህ አይደል እንዴ የአንድነትን ሀይል አሳየኝ ያልከኝ? 

እኔ፦ ማለት?

ሰካራሙ ሰይጣን፦ አየህ እነዚህ የምታያቸው አምስቱ ጣቶቼ ሙሉ ጣት ቢሆኑም ብቻቸውን ግን ምንም አይፈይዱም፤ ግን አንድ ላይ ሲሆኑ፣ እኔ ነኝ ያለውን ፈርጣማ ምድር ይደባልቁታል። አንድነት ሀይል ነው ማለት እንዲህ ነው። አለና ትኩር ብሎ እያየኝ፣ የምልህ አልገባህም መሰለኝ፣ ልድገምህ እንዴ ብሎ እጁን አሞልሙሎ ሲጠጋኝ፥ ጩኀቴን ሳስነካው ካለሁበት ብንን ስል፥ ልብሴ በላበት ርሶ ከህልሜ ነቃሁ።